አለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት ‘Nuclear Activity in Galaxies across Cosmic Time’ ሲንፖዚየም


አለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት ‘Nuclear Activity in Galaxies across Cosmic Time’ ሲንፖዚየም እና የአፍሪካ አስትሮኖሚ ማህበር የምክክር መድረክ ከመስከረም 27-30 በጁፒተር ሆቴል ሊካሄድ ነው፡፡

በአስትሮኖሚና በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በተለይም ለወጣቶች ከፍተኛ ተነሳሽነትን እየፈጠረ የሚገኘው አለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት (IAU) 100ኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል፡፡ ይህ ክብረ በዓል “100 years: under one sky!” በሚል መሪ ቃል ባለፉት አንድ መቶ አመታት ህብረቱ ያከናወናቸዉን ስራዎችና ስኬቶች እየገመገመና በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም ሲሆን፤ በኢትዮጵያም አመቱን በሙሉ ስለ አስትሮኖሚ ሳይንስ ግንዛቤ በሚፈጥሩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ አልፎም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የአለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት 356ኛ ሲንፖዚየም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴሩን ጨምሮ በርካታ የስራ ሃላፊዎች ፤ ከ30 የዉጪ ሃገራት ወደ 160 የሚጠጉ አለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ፤ ኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎችና ባለድርሻ ተቋማት ስለ አስትሮኖሚ እና ስፔስ ሳይንስ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡ ሲንፖዚየሙ ከመካሄዱ በፊት ባሉት 2 ቀናት 4ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካንፓስ በዘርፉ የ2ኛ እና 3ኛ ዲግሪያቸዉን እየሰሩ ላሉ ተማሪዎች የእዉቀትና ክህሎት ስልጠና ይሰጣል፡፡ በዋንኛነት ስለ AGN (Active Galactic Nucleus) ዉይይት የሚደረግ ሲሆን፤ አዲስ ስለተገኙ የህዋ አካላት እንዲሁም ከ AGN ጋር በተገናኘ የተመረጡ 7 አርዕስቶችም የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ ለ10 የህዝብ ትምህርት ቤቶችም በተግባር የታገዘ አስትሮኖሚ ሳይንስን የማስገንዘብ ስራ ይሰራል፡፡ አለም አቀፉ ሲንፖዚየም በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመካሄዱ መጠን በአስትሮኖሚና በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ከአለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ልምድ ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሲንፖዚየሙ በኋላ ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችም ስለ አስትሮኖሚ ሳይንስ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ የሚሰራ ሲሆን በተለይም ለ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ስልጠና ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም እና የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ጉብኝትም አንዱ መርሃ-ግብር ነው፡፡ የአለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት ከዚህ ቀደም በሳይንሳዊ መለያቸው HD16175 የሚባል ኮከብና HD16175b ተብሎ የሚታወቅ ፕላኔት ኢትዮጵያ እንድትሰይም እድል መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ከሲንፖዚየሙ ጎን ለጎንም የአፍሪካ አስትሮኖሚካል ማህበር (AfAS) የአስትሮኖሚ ሳይንስ በአፍሪካ ያለዉን ተደራሽነት ለማስፋት ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ማህበር እንዲፈጠር ጥልቅ ሳይንሳዊ ዉይይት የሚያደርግ ይሆናል፡፡ የአስትሮኖሚ ሳይንስ በአፍሪካ እንዲያድግ ስትራቴጂ የሚቀረፅበት መድረክ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ ይህንን መድረክ የምስራቅ አፍሪካ አስትሮኖሚ ለልማት ማስተባበሪያ ፅ/ቤት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር አዘጋጅተዉታል፡፡